የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ [ሸንጎ] ኦፊሴላዊ ድረ ገፅ

b'masf'rara

በማስፈራራትና በዛቻ የሕዝብ ትግል አይቆምም

ቢሆን ይሆናል ባይሆን አይተነው፣
  እንሄዳለን አደባይተነው።                      

 

በማስፈራራትና በዛቻ የሕዝብ ትግል አይቆምም

ቢሆን ይሆናል ባይሆን አይተነው፣

እንሄዳለን አደባይተነው።

በዚህ አይነቱ ስንኝ የታጀበ የእልቂት ፉከራና ዛቻ አባይ ጸሃዬና ስዩም መስፍን የተባሉት ቀንደኛ የሕወሀት ወንጀለኞች በብዙሃን የመገናኛ መድረክ ላይ ከ40 ደቂቃ በላይ በሰጡት ማብራሪያ የተደመጠ የሰሞኑ የሽብር መልእክት ነበር።እነዚህ የሕዝብና የአገር ጠላቶች ድርጅታቸው በሚመራው መንግበሥት ላይ የደረሰውን የፖለቲካና ማህበራዊ ክስረት ተመርኩዘው ካደረባቸው ስጋት በመነሳት ሕዝቡን ያልነቃ፣ዃላ ቀርና ለውጭ ሃይሎች ያጎበደደ ያቀጣጠለው ግርግር ነው ብለው የስድብና የንቀት ናዳ ሲያወርዱበት፣ የሕዝቡን እሮሮ የሚያጋልጡትንና የሚታገሉትን በውስጥና በውጭ የሚገኙትን የለውጥ ሃይሎችን እንደማንኛውም አምባ ገነን ስርዓት ጥላሸት እያለበሱ ከጥያቄው ለማምለጥ ሲውተረተሩ ተደምጠዋል ። የነፍጠኞች፣ የትምክህተኞች፣የጠባቦችና የውጭ አገር ሴራ አስፈጻሚዎች በማለት ከሰዋል።በዚህም ብቻ አላቆሙም እራሳቸውን የአንድነት፣የሰላም፣የእድገት፣ የእኩልነት፣የዴሞክራሲ  ጠበቃና  ፈጣሪዎች  እንደ ሆኑ አድርገው አቅርበዋል። እነሱን መቃወም ማለት ደግሞ ሰላም ማናጋት፣እድገትን መጎተት፣አንድነትን ማፍረስ፣እኩልነትን ሽሮ አንዱ ጌታ ሌላው ባሪያ የሚሆንበትን ስርዓት መልሶ ለማምጣት  የሚደረግ አድማና ሴራ ነው በማለት ጥፋቱን ከራሳቸው ላይ አውርደው በሌላው ላይ ለመጫን ሞክረዋል።ለመሆኑ እድገት ሲባል የሕዝብ አስተያየትንና ንቃትን ያካተተ አይደለምን? ሕዝቡን ዃላ ቀር፣ደደብ ብለው ከተሳደቡ በሕዝቡ ንቃት ለውጥ አልመጣም ማለት ነው።

አደገ ተመነደገ የሚሉት ኤኮኖሚ ከሕንጻና ከከበርቴው መዝናኛ ቦታዎች  መስፋፋት  ያለፈ  አይደለም ማለት ነው።የውጭ ዘራፊዎች ካቋቋሙት ድርጅት የዘለለ ለውጥ በአገሪቱና በሕዝቡ ኑሮ ብሎም ግንዛቤና ንቃት ላይ አላመጣም ማለት ነው። እውነተኛ እድገት አለመኖሩን በደም ፍላት ያስተላለፉት መልእክት ፈልቅቆ አወጣው።ከአፍ ከወጣ አፋፍ! ይሏል ይህ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለበትን ኑሮና መከራ እያወቀውና እየተቃወመው ጥያቄና ቅዋሜውን ከዃላ ቀርነት፣ ከድንቁርናው የመነጨ ድክመት ነው በማለት የሕዝብን ችሎታ በማኮሰስ የሚያደርገው ትግልም የደደቦች ተግባር ነው በማለት አርክሰውታል።ሕወሀት ንቀትና እብሪት በዛሬው በነዚህ ሁለት ጨካኞች የተጀመረ ሳይሆን የፈጠሩት ድርጅት ከተመሰረተበት ከዛሬ አርባ ዓመት ጀምሮ ሲዳብር የኖረ፣አሁን አገራችን ካለችበት ውድቀትና አደጋ ውስጥ የነከረ መመሪያና ስልት ነው። አገርን ለመበታተን፣የሕዝቡን አንድነት ለማናጋት ዘርን፣ ሃይማኖትን፣ቋንቋና ክልልን መሳሪያ አድርጎ የተጠቀመው ህወሃት/ኢህአዴግ እንጂ ሕዝቡና ለዴሞክራሲ ለውጥ፣ለፍትህና ለእኩልነት የተነሳው ሕዝባዊ ሃይሉ እንዳልሆነ እነሱም ሌሎቹም ያውቁታል።ሕዝባዊ ሃይሉ ችሎ ችሎ የግፉ መጠን ገደቡን ሲያልፍ በቃኝ ብሎ ተነስቷል፤ይህን የሕዝብ
 
መነሳሳት ለመቅጨት እነዚህ ሁለቱ አንጋፋ ወንጀለኞች የድርጅታቸውን የማስፈራሪያ በትር መዘው ብቅ አሉ፣ያም እኛ ከሌለን አገር አትኖርም፣እኛ ከሌለን እርስ በርሳችሁ እንደ ሩዋንዳና ዩጎዝላቪያ ትተራረዳላችሁ፣እንደሶማሊያ ትበታተኑና የትርምስና የእልቂት ሜዳ ትሆናላችሁ፣ልታንሰራሩም አትችሉም የሚል አረመኔያዊ ትንቢት መሳይ ማስፈራሪያ ነው።

ከቀውሱ ውስጥ ግን እራሳቸውን አልቀላቀሉም፤ምክንያቱም ፈርጥጠው ሊወጡ የሚችሉበትን ቦታና በር አመቻችተዋልና! ከዛም በተረፈ በስሙ ተጠቅመው ስልጣን ላይ ወጥተው በአውሬው ክርናቸው የሚደቁሱትን የትግራይን ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ነጥለው በመሳሪያነቱ ለመቀጠል እንዲችሉ የሽብር ቅስቀሳ አድርገውበታል።ብዙሃኑ የትግራይ ሕዝብ በጎሰኛ አስተሳሰብ ተነሳስቶ በሌላው ወገኑ ላይ እንዲነሳና ለነሱ የጥፋት ስርዓት አገልጋይ እንዲሆን አሁንም በዚህ መልእክታቸው አስተጋብተዋል።

በተለያዬ አጋጣሚ እንዳሳየው ሁሉ አሁንም የትግራይ ሕዝብ ዝም ሊላቸውና ለውጥናቸው ተገዢ መሆን አይኖርበትም፤ወግዱ፣አልታለልም፣የእስከዛሬው ይበቃል ሊል ይገባዋል።ህወሃት ያዘጋጀው መቅሰፍትና የጥፋት አደጋ የትግራይንም መሬትና ተወላጅ የሚምር አይደለም።ተያይዞ ገደል እንዳይሆን ይህን በስማቸው የሚነግድ የአገር ፍቅርና ሰብአዊ ስሜት የሌለው ጨካኝ ቡድን ቦታና ዕድል ሊነፍገው ይገባል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲባል የትግራይን ሕዝብ የሚነጥል አይደለም።የኢትዮጵያ ሕዝብ ተበደለ ሲባልም፣ በስርዓቱ ያልተበደለና ያልተሰቃዬ ባለመኖሩ የስርዓቱ አገልጋይ ያልሆነ የትግራይም ተወላጅ የሚጋራው ዕጣፈንታ ነው።የተጨቆነው ሕዝብ ጥያቄው አንድ ነው፤ያም ግፈኛው ስርዓት እንዲያከትም የሚጠይቅና የሚታገል ነው።

በዚያ የነጻነት ትግል ጎራ ውስጥ የትግራይም ተወላጆች አሉበት። ብዙሃኑ ከአጥፊው ቡድን ጋር ሳይሆን ከትግሉ እንዲቀላቀል የሚያደርግ ስራ በስፋት መሰራት አለበት።የወንጀለኞች መጠቀሚያ እንዳይሆን የሚያግዝ ስልት መነደፍ ይኖርበታል።ህወሃት የሕዝቡን አንድነት ለማኮላሸት በሌሎች አሳቦ የሚስጥር ጥቃት በትግራይ ተወላጆች ላይ እንደሚያዘጋጅና እስከመፈጸም ሊጓዝ እንደሚችል ከወዲሁ መገንዘብና ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው።ከአጥፊው ቡድን ጋር ወግነው የሚቆሙት ከማንኛውም ማህበረሰብና ጎሳ የተውጣጡ የስርዓቱ ተጠቃሚዎች የሆኑት ብቻ ናቸው።ጥቅም አይንና ህሊናን ይሸፍናልና በዚያ መጋረጃ ውስጥ ተተብትበው የተያዙት የሁሉም ጎሳ ተወላጆች ናቸው፤ካለነርሱ ትብብር ህወሀት/ኢህአዴግ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ምድር ላይና በሁሉም ሕዝብ ጫንቃ ላይ የመከራ ቀንበሩን ሊያሰፍር አይቻለውም ነበር።

የህወሓት/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት አገራችንን ለሩዋንዳና ለዩጎዝላቪያ እልቂት እያዘጋጁዋት መሆኑን በገሃድ ተናግረዋል፤ኢትዮጵያ በነዚህ አናሳ ወንጀለኞች ውሳኔ የምትፈራርስ ሳይሆን በሕዝቡ የቆረጠና የተባበረ ትግል ለዘለዓለም ተከብራ የምትኖር አገር መሆኗን ማሳየት አለብን። በነሱ የጥፋት ፉከራና ዛቻ ቅስማችን ሊሰበር አይገባውም፤የሕዝቡ ትግል ፈሩን ሳይለቅ፣ከተዘጋጀው የመጠፋፋት ወጥመድ ውስጥ ሳይገባ፣ ለዘላቂ ዴሚክራሲያዊ ስርዓትና የሕግ የበላይነት፣ለሕዝብ አብሮ መኖርና ለአገር አንድነት የምናደርገውን ትግል በተቀናጀ መልኩ ከግቡ ማድረስ የየአንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ድርሻ ሲሆን ይበልጥ ደግሞ የፖለቲካ ምህዳሩን እንለውጣለን ብለው የተሰለፉት ሃይሎች አላፊነት ስላለባቸው  ተባብረው ሊቆሙ ይገባቸዋል፤እርስ በርስ እየተናቆሩ የሚጓዙበት ጊዜው አልፏል፡፤እንደ ህወሓት/ኢሕአዴግ ስርዓት ሰሚ አልባ ላለመሆን ከተፈለገ በትናንትናው የጎሳና የክልል ድርጅታዊ አባዜ መንጎድ የለብንም፤አገራችን
 
ከዚህ አደገኛ ደረጃ ላይ የደረሰችውና ለበለጠም አደጋ የምትጋለጠው በጎሳና ክልል ስሜታዊ አወቃቀር ተነጣጥለን ከተሰለፍን ነው።

ያ አካሄድ እስከዛሬ ድረስና ለወደፊቱም ሕወሀት/ኢህአዴግ ላዘጋጀልን የጥፋት መቅሰፍት ተመቻችተን እንድንገኝ ያደርገናል። በሰው ልጅነታችን፣በኢትዮጵያዊ ዜግነታችን እጅ ለእጅ ተያይዘን የመጣውን አደጋ ከመታደግ የተሻለ ምርጫ የለንም።የሕወሀት/ኢህአዴግን የጥፋት ቅስቀሳ ወደ ለውጥ አቅጣጫ ልንመራው ይገባል።

በቅርቡ አስራ ስድስት የሚሆኑ በአገር ውስጥ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱት ድርጅቶች የሰላምና እርቅ ጉባኤ እንዲጠራ ማሳሰባቸው ይፋ ወጥቷል።እርምጃው ቀና ቢመስልም እነማን እንደሆኑ ዝርዝራቸው ስላልወጣና ስለማይታወቅ ድርጅቶቹ በስርዓቱ ተጠፍጥፈው የተቋቋሙ ወይም የተደቀሉ ይሁኑ አይሁኑ የሚታወቅ ነገር  የለም።በተጨማሪም የሰላም አጋርና ጸር  የሆነውን ለይተው ማወቅና ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ውይይት ላይ የመድረክ፣የሰማያዊ፣የመኢአድና የሌሎቹም አገር አቀፍ ድርጅቶች ህልውናና ተሳትፎ አልታወቀም።በስርዓቱ መዳፍና ፈቃድ የሚሽከረከሩት ብቻ ለይስሙላ የሰላም ውይይት ከቀረቡ ውጤቱ እዛው በዛው ይሆንና ፣አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ ሆነው የሚያሳልፉት ውሳኔ  የቤተሰብ መተቃቀፍ ይሆናል።

በተጨማሪም የሰላሙ ውይይቱ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያበቃ እንጂ በሽርፍራፊ ለውጥ ያለው ስርዓት    እንዲቀጥል    ለማድረግ    እንዳልሆነ    በቅድሚያ    መገንዘብ    ይገባል።    የሰላም    ውይይቱ በሕጋዊነትተመዝግበው የሚንቀሳቀሱት ብቻ ሳይሆኑ በህወሀት/ኢህአዴግ ተፈርጀው የታገዱትና በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚንቀሳቀሱትን የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማህበራትና የታወቁ ግለሰቦችን፣ የሚያጠቃልል መሆን ይኖርበታል። ያ ካልሆነ ለሚያስተማምን ሰላምና ሁሉን ላካተተ እርቅ አያበቃም።

ለሰላሙ ውይይት በር መክፈቻው የታሰሩትን መልቀቅ፣የታፈነው የሚዲያ ነጻነት መረጋገጥ፣የመደራጀትና የመሰብሰብ፣የዲሞክራሲ    መብቶች    መከበር፣በሕዝቡ    ላይ    የጥቃት    እርምጃ    እንዲፈጽም    የተሰማራው የመንግሥት የጦር ሃይልና የታጠቀ ቡድን ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲመለስ ፣ጉዳት ለደረሰባቸው ካሳ እንዲከፈላቸው፣  ተጠያቂው  በሕግ  እንዲጠየቅ  ማድረግ  ለነገ  የማይባል  የሂደቱ  መግቢያ  ቁልፍ  ነው። እቅዱ በሕዝቡ ተሳትፎና ፍላጎት እንጂ በጥቂት የፖለቲካ ድርጅቶችና በቀውሱ ባለቤት በሆነው አምባገነን ቡድን ፈቃድና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆን አይኖርበትም።

ስለሆነም የውስጥና የውጭ የሚለው ግድግዳ ተንዶ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት እንዲሆን ማድረጉ አማራጭ የለውም።አንዱን አቅፎ ሌላውን ማራቅና ማግለል ለ25 አመት ከተመለከትነው ተመሳሳይ የጥፋት አሮንቃ ውስጥ መዳከር ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውንና በመፈጸም  ላይ ያለውን ግፍና ጭፍጨፋ እያወገዘ፣ ወንጀሉን የፈጸሙትና ያስፈጸሙት በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ይጠያቃል።ሕዝቡ ለመለያየት የተቀመረለትን የጥፋት ጎዳና እንዳይከተል እያሳሰበ እጅ ለእጅ ተያይዞ ጥቃቱን እንዲመክት ጥሪ ያደርጋል።የሕዝቡን ብሶት ለዓለም ማህበረተሰብ ለማሰማትና በስርዓቱ ላይ ተአቅቦ እንዲጣል ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ እየገለጸ፣በውጭ አገር የሚገኙት የፖለቲካ ድርጅቶች፣
 
የሲቪክ  ማህበራትና ተቋማት  እንዲሁም  ግለሰቦች  በዚህ  ፈታኝ  ወቅት  ላይ  ከመቸውም ጊዜ  በበለጠ የአንድነት ትግላቸውን ማካሄድና እርዳታ ለሚያስፈልገው ወገናቸው ገንዘብ የማሰባሰቡን ሥራ እንዲቀጥሉበት ጥሪ ያደርጋል።

የተከሰተውን አደጋ ለመመርመርና የአገራችንን የወደፊት አማራጮ ለመመካከር በአስቸኳይ ጉባኤ መጠራት እንዳለበት በማመን ሸንጎ የበኩሉን ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ለማሳወቅ ይወዳል፡፤ በዚህ በታሰበው ጉባኤ ላይ እንዳለፈው ጊዜ ምክንያት እየፈጠሩ  ማፈግፈግ አገራችንና ሕዝቡ የተደቀነበትን አደጋ ጥልቀትና አጣዳፊነት አለመረዳት ይሆናል።አላፊነት የሚሰማቸውና አደጋውን የተረዱ ጥሪውን አክብሮ ከመገኘት ሌላ አማራጭ የለም።ስለሆነም ሁሉም ጥሪውን አክብሮ ይገኛል የሚል እምነት አለን።

የተሰናዳልንን የጥፋት ሴራ በአንድነት እናክሽፈው!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ