የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ [ሸንጎ] ኦፊሴላዊ ድረ ገፅ

brasu lay

በራሱ ሕዝብ ላይ የሚዘምት መንግሥት ወይስ አሸባሪ

 

ሸንጎ ገና ከጅምሩ አንስቶ ህወሃት/ኢሕአዴግ የተሰኘው አገር አጥፊ ቡድን ለምን ዓላማና ለማንስ ጥቅም እንቀደቆመ ሲገልጽ ቆይቷል፤ከዚህ መግለጫ በፊትም “የጥፋት ደወል ሲያንቃጭል”በሚል እርእስ ስርዓቱ የደረሰበትን ደረጃና ሊቀጥል የሚችለውንም አደጋ አሳይቷል።
በትናንትናው ዕለት በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ፣እንኳንስ ለሕዝብ ቆሚያለሁ እያለ የሚዋሽ መንግሥት ቀርቶ የውጭ ወራሪ ሃይልም ይፈጽመዋል ተብሎ በማይጠበቅ መልኩ የራሱን ሕዝብ ከአየርና ከመሬት ዓልሞ ተኳሾች፣ለአገር መከላከያ ተብሎ በሕዝብ ሃብት የተቋቋመና ደመወዝ የሚከፈለውን ወታደር ሳይሆን ሆድ አደር ሰራዊት አዝምቶ በእጁ ግፋ ቢል የሰላም ምልክት የሆነ ለምለም ቅጠል ጨብጦ ብሔራዊ የባህል በዓል ለማክበር በወጣው በሚሊዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ላይ የጥይት ዝናብ አዝንቦ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሲገል በሽህ የሚቆጠሩትን ደግሞ በማቁሰል ለአካለስንኩልነት ዳርጓቸዋል።
በዚህ የእልቂት ዘመቻ ሰለባ የሆነው አብዛኛው ወጣት ሲሆን አዛውንትና አሮጊቶች፣የዕድሜ ክልልና ጾታ ሳይነጥለው ከአገሪቱ ክፍለ ሃገር ከጫፍ እስከጫፍ መጥተው የተካፈሉበት ነበር፤ምንም እንኳን በዓሉ የኦሮሞ ማህበረሰብ ባህላዊ በዓል ቢሆንም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኔም በዓል ነው በማለት ከአማራው፣ ከአፋሩ፣ከወላይታው፣ከኦጋዴው፣ ከጉራጌው፣ከጉሙዙ፣ከጋምቤላው፣ከኮንሶው፣ …ወዘተ እስላሙና ክርስቲያኑ ሃይማኖትና ቋንቋ ሳይለየው አንድ ላይ ለማክበር የተሰበሰበ ሕዝብ ነበር።ይህ የሕዝብ መቀራረብና መተሳሰብ ያስጨነቀው አገር አጥፊ ቡድን ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ሲለፋበት የኖረው የከፋፍለህ ግዛ መመሪያ እንዳልሰራለት በመገንዘብ አደርገዋለሁ ያለውን የእልቂት ዛቻ በትናንትናው ቀን በተግባር ገልጾታል።በዚህም ብቻ የሚያበቃ አይሆንም፤ ይህ ህወሀት መራሹ  ቡድን እንደሚጠረጠረውና እንደሚጠበቀው ኢትዮጵያን  አተረማምሶ ህዝቡንም አርሰ በርስ አፋጅቶ  አስከመሄድ የሚደርስ አጥፊ አጀንዳውን እውን እንደሚያደርገው ይህ የትናንቱ እርምጃው ጉልህ ማስረጃ ነው።
የሕዝቡ ታሪካዊ ግንኙነትና ትስስር በትናንትናው ዕለት ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ከወሎ ከአዲስ አበባ   ከኦሮሞው ወገኖቻቸው ጋር በዓሉን ለማክበር ቢሸፍቱ ሄደው ከኦሮሞው ወገናቸው ጎን የተሰዉት፣ ለፍቅርና ለአንድነት የከፈሉት የሕይወት ዋጋና ያፈሰሱት ደም  ለሕዝቡ በተለይም ለአማራውና ለኦሮሞው ማህበረሰብ እንደቆየው አብሮ መኖር ሲሚንቶና አሸዋ ነው። እነዚህ ማህበረሰቦች አገራቸው በውጭ ጠላት በተወረረችበትም ጊዜ ጦርሜዳላይ ተቃቅፈው ወድቀዋል፤ለእኛ መኖር የጋራ ዋጋ ከፍለዋል።በዚህ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ አንድ የሃያሁለት ዓመት ወጣት፣ ሊመረቅ የተቃረበ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነ ልጃቸውን ያጡ እናት “ሃዘኔ ገደብ ባይኖረውም፣ካንጀቴ ባይወጣም፣ አንዱ ልጄ፣ጦሮ ይቀብረኛል ያልኩት ልጄ እንደ አጋዚ ወታደር ወገኑን ለመግደል ወጥቶ የቀረ ሳይሆን ከወገኑ ጎን ተሰልፎ በመሞቱ አላሳፈረኝም፤ይብላኝ!  ወገኑን ለመጨፍጨፍ ለተሰለፈው ለአጋዚና ለመንግሥት ሆድ አደር ወታደር እናት ለሆነችው!” በማለት የልጃቸውን መሞት በኩራት ተቀብለዋል።ከዚህ የበለጠ ፍቅር፣የአንድነትና የአብሮነት ምልክት ምን አለ?በሌለ አቅም ስድስት መቶ ኪሎሜትር ተጉዞ ከኦሮሞው ወገኑ ጋር በጥይት ተመቶ ሲያሸልብ አንድ ህይወቱን አሳልፎ ሲሰጥ ከዚህ በላይ ኦሮሞው  ከሌላው ለኢትዮጵያዊነቱ  ምን ማረጋገጫ ይፈልጋል?
እርግጥ ነው ለሰላም.ለአንድነት፣ለአብሮነት መሞት ያኮራል።ለሕዝብ ጠላት ለሆነ አረመኔ ሥርዓት ተቀጥሮ በወገኑ ላይ እልቂት ለሚፈጽም ሆድ አደር ቅጥረኛ ዘመድ አዝማድ፣ልጅ፣ሚስት ቀርቶ ጎረቤት ያሳፍራል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ(ሸንጎ)የህወሃት/ኢሕአዴግ አገር አጥፊ ቡድን በወገኖቻችን ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ እያወገዘ፣በተቃዋሚው ጎራ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የቢሸፍቱን የአንድነት አርማ በመያዝ በመካከሉ ያለውን መናኛ ልዩነት አሶግዶ በአንድ እንዲቆም አሁንም ሳይሰለች ጥሪውን ያቀርባል።ሕዝቡ ጎሳ፣ቋንቋና እምነት ሳያግደው፣የቦታ እርቀት ሳይገድበው ለአንድ ሕዝባዊ በዓልና ዓላማ እንደተሰለፈው ሁሉ በውጭና በውስጥ የሚገኘውም ሃይል አብሮ መቆም አለበት።
ይህ በወገኖቹ ላይ ጭፍጨፋ የሚፈጽም ቡድን በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት አስከባሪ ድርጅት ውስጥ አባል እንዲሆን የድጋፍ ድምጽ የሰጡትን የውሳኔያቸው ውጤት ምን እንደሚመስል እንዲያውቁት ማድረግ ይገባል።በተጨማሪም የዚህ እኩይ መንግሥት ምንነት ሲገለጽላቸው የቆዩትና በዝምታ የተቀመጡት የውጭ አገር መንግሥታትና ድርጅቶች የሚሰጡትን ድጋፍ እንዲያነሱ መጠየቅ፤ካላነሱና ግንኙነታቸውን ካልመረመሩት እነሱም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለተፈጸመውና ለሚፈጸመው በደል ተጠያቂዎች እንደሚሆኑ መግለጽ ተገቢ ነው።እርዱን ብሎ ከመጠየቅና ተነጣጥሎ በጓዳ በር እየገቡ ከመለማመጥ በእራሳችንና በሕዝባችን ተማምነን፣እጅ ለእጅ ተያይዘን የተጀመረውን ሕዝባዊ ትግል ማፋፋምና ከግብ እንዲደርስም ማድረግ ይኖርብናል።
የህወሃት/ኢህአዴግ ተብየው ቡድን የሚቀጥለው እርምጃው አጥፍቶ መጥፋት ስለሚሆን መውጫ ቀዳዳ እንዳያገኝ በሩን መዝጋት ያስፈልጋል።ለዚህ ሁሉ የገንዘብና የቁስ አቅርቦት ወሳኝ ነው።ይህ ዝግጅት  ከቅስቀሳው ሥራ ጎን ለጎን መከናወን ያለበት ጉዳይ ነው። አሁን የምንሠራበት እንጂ የምናወራበት ጊዜ አይደለም።ያለንበት ወቅት የነጵነት  ትግሉ የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ ቢሆንም ዘረኛውን ስረአት ደምስሰን የህዝባችንን ድል እውን ለማድረግ  እጅግ የተቃረብንበት ነው ::
የጋራ ዓላማችን ይህን እኩይ መንግሥት አውርዶ በሁሉን አቀፍ  የሽግግር መንግሥት መተካት መሆን አለበት እንጂ በሽርፍራፊ ለውጥ ተሞዳሙዶ ለቀጣይ እልቂት ሰለባ መሆን አይገባውም። መጭው ዘመንና ስርአት ከፋፋይ ፖለቲካ አክትሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአኩልነት የሚታይበትና የሚኖርበት  አንድነትና  አብሮነት በክብር የሚዳበሩበት እንዲሆን እንታገላለን
አንድነት በአንድነት!!
የቢሸፍቱ እልቂት ለኢትዮጵያ ትንሳኤ የተከፈለ መስዋእትነት ነው!  
መስከረም 23፣2009 (October 3, 2015)