የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ [ሸንጎ] ኦፊሴላዊ ድረ ገፅ

Shengo Dimts

Shengo Dimts (10)

በአንድ ከባቢ የሚኖሩ ሰዎች ድንገት ሰፈራቸው በእሳት ጋይቶ የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ፣ምናልባት ብንድን ብለው ወደሌላ አቅጣጫ ካለው ሰፈር ለመጠለል ሲሮጡ፣ ከዛኛውም ሰፈር እንደዚሁ እሳት ተነስቶ ኑሮ፣ ብዙ ሰዎች ወደዚህኛው ሰፈር ሲገሰግሱ መሃል ቦታ ላይ ተገናኙ። ከመካከላቸው አንዱ የእኛ ሰፈር በእሳት ጋይቶ ለመጠለል ወደ እናንተ ሰፈር እየመጣን እናንተ ደግሞ በእጥፍ ቁጥር ወደእኛ እየገሰገሳችሁ ነው፡፡ ለመሆኑ የደረሰብንን ጉዳት ሰምታችሁ እሳቱን ለማጥፋት ነው ወይስ እኛን ከመንገድ ላይ ተቀብላችሁ ልታስተናግዱን ነው ይኸ ሁሉ ሰው የመጣው? ብሎ የወዲያኛውን ሰፈር ኗሪ ጠየቀ። የተጠየቀውም ሰው ግር ብሎት የእሳቱ መነሳት እንዴት ከእናንተ ጆሮ ደረሰ? ለማጥፋት ልትተባበሩን ነው የመጣችሁት? ብሎ በመገረም መልሶ ጠየቀው።
ሁሉም ግራ ተጋቡና የየራሳቸውን ሰፈር መቃጠል እያነሱ ሲጨቃጨቁ በመገረም የሚያስተውሉ አንዱ አረጋዊ ሰው፤ምነው ወገኖቼ ተደማመጡ እንጂ! ሁለታችሁም እኮ እሳት ያባረራችሁ የእሳት በደለኞች ናችሁ። እንዴት መደማመጥ ይሳናችዃል? አንዳችሁ የሌላውን መቃጠል መረዳት ተስኗችሁ የእኔ ሰፈር ነው የተቃጠለው፣ የአንተ ሰፈር ሰላምና ከእሳት ነጻ ነው፤ መባባል አመጣችሁ? አንዱ የአንዱን መቃጠል መቀበልና ማወቅ እንዴት ይሳነዋል? ሰው ወዶ ቤቱንና ሰፈሩን አይለቅም። እሁለታችሁም ሰፈር እሳት አለ፣የሁለታችሁም ቤት እየጋየ ነው።እሳት እሳት ነው። አንዱን አጥፍቶ ሌላውን አይምርም።እሳት አንዱን የሚያቃጥል ሌላውን የሚያበርድ አይደለም።በሁለታችንም ሰፈር የተነሳውን እሳት የለም ብሎ መካድ ከለኮሰው ጋር ተመሳጥሮ ጉዳትን አለማወቅና አለመቀበል ነው። እሳት ሁላችንንም እያጠፋ ቤት ንብረታችንን እያወደመ ነው። ይልቁንስ አንድ ላይ ሆነን የለኮሰውን እንፈልግና ለሕግ እናቅርብ፤ ለወደፊቱም እሳት እንዳይነሳ ማገዶ ከሚሆን እንጨት የተሻለ ቤት ለመስራትና ከአደጋው ለመገላገል መላ እንምታ በማለት በሳል አስተያየትና ምክር አቀረቡ።
እኛ ኢትዮጵያውያንና ቀደም ኢትዮጵያውያን የአሁኑ ኤርትራውያን ሕዝቦች በምንኖርበት አገር የሰፈኑት አምባገነን ስርዓቶች የሚፈጁ እሳቶች ናቸው። ሁላችንም የሚፈጽሙት ግፍና በደል ሰለባዎች ነን፡፤ሁላችንም በተመሳሳይ አምባገነንና ጸረ ዴሞክራሲያዊ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች በሆኑ፣ ተደጋጋፊ ስርዓቶች ውስጥ የምንማቅቅ፣ ለስደት የተዳረግን፣ አንድ አይነት ፍላጎት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ እምነት መልክ፣ ስም ስነልቦና ያለን ዜጎች ነን።
ሁለቱ አምባገነን ስርዓቶች በሚቆጣጠሩት መሬት ውስጥ ለሚኖረው ሕዝብ የሚያቃጥሉ እሳቶች ናቸው። የእነዚህን ስርዓቶች ክፋትና በሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን በደል መካድና እንደ በጎ አድራጊ መቁጠር፣ወይም አንዱን በማርከስ ሌላውን በማንገስ ወይም በማወደስ ፣የራስን በደል እያጎሉ የሌላውን ሕዝብ ስቃይ እንደሌለ መካድ በሰው ቁስል ላይ እንጨት እንደመክተት ይቆጠራል። ለማይረባ ጥቅም ሲሉ ሌላውን መሰል ሕዝብ አሳልፎ መስጠትና ችግሩን አለመገንዘብ በታሪክ ያስጠይቃል። ከጠላት የበሉት በሶ፣ ይወጣል ደም ጎርሶ እንደሚባለው ፣ሕዝብ ከጠላው ስርዓትና መሪ ጋር አብሮ መቆም ሲገረሰስ አብሮ መጨፍለቅ እንደሚሆን ማሰቡ ብልህነት ነው። ከአንድ ሕዝብ ከጠላው መሪና ስርዓት ጋር ከመሰለፍ ከሕዝብ ጎን ቆሞ በደሉን ቢያውቁለት የተሻለና በድል ማግስት የሚያኮራ ይሆናል። ከማፈርና አንገት ከመድፋት ያድናል።
በተመሳሳይ ደረጃም ለጥቂት ጊዜአዊ ጥቅም ሲሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ህወሃት መራሹን አምባገነን ስርዓት ዴሞክራቲክ አድርጎ ማቅረብና በኤርትራ መሬት ላይ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመት በፈላጭ ቆራጭነት በስልጣን ላይ የተቀመጠውን የሻእብያ መንግሥትና መሪ ዴሞክራትና አርቆ አሳቢ፣ ለሕዝብ ተቆርቋሪ አድርጎ ማቅረብ የሚያስተዛዝብ ጉዳይ ነው።
እነዚህን የሕዝብ የመከራ ምንጭ የሆኑትን አምባገነን ስርዓቶች በህዝብ ላይ የሚያደርሱትን ግፍ  መካድ፣ ብሎም ለነሱ ድጋፍ መስጠትና ያልሆኑትን ናቸው እያሉ መካብ የዓለም ሕዝብ የሚያውቀውን እውነት መካድ ማለት ነው።
ከኢትዮጵያና ከኤርትራ በየቀኑ በቀይባህርና በሜዲትራንያን ባሕር አደጋን ለመጋፈጥና ካሉበት ኑሮ የነጻነት ሞትን መርጠው የሚሰደዱትን እንደ ቅንጡ አገር ጎብኝ በመቁጠር ከአገራቸው የሚያባርራቸው ምክንያት የሆነ መንግሥትና ስርዓት የለም ብሎ ማቅረብ ነው።
በሁለቱም አምባገነኖች የሚረገጡት ሕዝቦች የጋራ ችግር አለባቸው፤ ያም የመልካም ስርዓት አለመኖርና  ቀና መሪ አለመኖር ነው። አለዚያማ እንዴት ሰው አገሩን፣ ወገኑንና ቤተሰቡን ጭምር ጥሎ ለመድረሱ ዋስትና በሌለው መንገድ ወደ ማያውቀው አገር ይሰደዳል?  ድህነት ነው ቢባልም፣ድህነቱ በምን ምክንያት ተፈጠረ ብሎ መጠየቅ ይገባል። ለዚያ ደግሞ መልሱ ከስርዓቱ ጋር የተያያዘ ሆኖ ይገኛል።
የኢትዮጵያና የአሁኗ ኤርትራ ሕዝብ አብሮ በአንድ አገር ልጅነት ለዘመናት ኖሯል፡፤ወደፊትም መልሶ ሊኖር ይችላል።በሕዝብ  የሚመረጥ፣ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ ፣ሕዝብ የሚያቀራርብ ስርዓት እንዲሰፍን፣ አብሮ ለመኖር የሚያስችለውን ፍላጎት እንዲዳብር የሚሻ ዜጋ አሁን ከሕዝቡ ጎን ይቆማል እንጂ ከጨቋኝ ጋር አይሞዳሞድም። ለአምባገነኖች ድጋፍና እውቅናም ሰብሳቢም አሰባሳቢም  አይሆንም።
በሁለቱም ሕዝቦች ላይ የተጫኑትን ጨቋኝና አምባገነን አገዛዞች ለውጦ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመመስረት፣ በርግጥም የህዝብን ልዖላዊነት እውን ለማድረግ፣ በሁሉም በኩል ያሉ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች በጋራ በመቆምና በመተባበር የህዝብ ወገንተኛነታቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ(ሸንጎ) አመለካከት በኤርትራና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩት ዜጎች የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ናቸው፣በስልጣንም ላይ ያሉት አምባገነኖች እንደዚሁ።
ሁለቱም ሕዝብ በማራራቅና በማለያየት ስልጣን ላይ የተቀመጡት አምባገነኖች ዕድሜ ሲያጥር ካለፍላጎታቸው ተገደው የተለያዩት የሚቀራረቡበትና በሰላም የሚኖሩበት ዕድል ይፈጠራል ብሎ ያምናል።የሁሉንም ችግር ለመፍታት የሚያስችል ስርዓት እንዲመጣ በህብረት መታገል ተገቢ ነው ብሎ ያምናል እንጂ ለትንሽና ጊዜያዊ ጥቅም ሲል ህዝብን አሳልፎ አይሰጥም።
ህወሃትና ኢሕአዴግን የሚደግፉ ኤርትራውያንም ሆኑ ሻብያንና ኢሳያስን የሚደግፉ ኢትዮጵያውያን ማሰብ ከሚገባቸው ነገር ውስጥ አንዱ የህዝብ መሰረታዊ መብት መከበር ከጊዚያዊ የፖለቲካ ድግፍ ማሰባበብ ባለፈ ሁኔታ ሊታይ የሚገባው ክቡር ጉዳይ እንደሆነና በመንገዳገድ ላይ ያለው የነዚህ አምባገነኖች ስርዓት ሲወድቅ ምን ይደርስብኝ ይሆን? የእኔ ተግባር ሕዝብ ሊያራርቅ ወይም ሊያቀራረብ ይችላል ወይ?ብሎ መጠየቅና መንገዳቸውን
ማስተካከልና ማረም እንደሚኖርባቸው ነው።

በየቦታው ያሉ አምባገነኖች በህዝብ ጣምራ ትግል ይወገዳሉ!!
የአንዱ ጭቁን ሕዝብ በደል ለሌላው ጭቁን ሕዝብ በደሉ፣የአንዱ ጭቁን ሕዝብ ድልም ለሌላው ጭቁን ሕዝብ ድሉ ነው።

በአንድነት፣ለአንድነት!!!

Published in Shengo Dimts
Written by
Read more...

Published in Shengo Dimts
Written by
Read more...

Published in Shengo Dimts
Written by
Read more...

Published in Shengo Dimts
Written by
Read more...

Published in Shengo Dimts
Written by
Read more...